አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥትና መሪው ብልጽግና ፓርቲ ለቀጣናው ሰላምና ብልጽግና ከሩዋንዳ ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህ በ2ኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ለመታደም ትላንት ምሽት አዲስ አበባ ከገቡት የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ዌላርስ ጋሳማጌራን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ብልጽግና ፓርቲ ለሰላምና ኢኮኖሚ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት አቶ አደም ፥ በመጀመሪያው ጉባኤ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆኗን ገልጸው ፥ ፓርቲው በመጀመሪያ ጉባኤው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በስንዴ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሩዝና ሌሎች ምርቶችም እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት አሁን ላይ ከ50 በላይ ከተሞች ላይ እየተተገበረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አደም ፋራህ የገጠር ኮሪደር ልማትም መጀመሩን ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለግብርና፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማዕድንና ለዲጅታል ዘርፎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የዜጎችን የልማት ጥያቄ እየመለሰ መሆኑንም አንስተዋል።
ፓርቲው ሰላምና ብልጽግናን ቀዳሚ ትኩረቱ አድርጎ እየሠራ ነው ያሉት አቶ አደም ከሩዋንዳ ጋር በፓርቲ ለፓርቲና መንግሥት ለመንግሥት ትብብር እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ለሁለትዮሽ፣ ለቀጣናዊና አህጉራዊ ሰላምና ብልጽግና በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉም ነው ያሉት።
የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ዌላርስ ጋሳማጌራ በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ በአስደናቂ የለውጥ ጉዞ ላይ መሆኗን አንስተዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉና የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በመፈጸም እያስመዘገበ ያለውን ስኬትም ዋና ፀሐፊው አድንቀዋል።
ሁለቱ ሀገራት በፓርቲ ለፓርቲ እና መንግሥት ለመንግሥት በበርካታ መስኮች ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡