የሀገር ውስጥ ዜና

ሆቴሎች የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ እንግዶችን ለማስተናገድ …

By Melaku Gedif

January 31, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር አስታውቋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን እንደገለጹት÷ ለጉባዔው የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ 40 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ተለይተዋል፡፡

ሆቴሎቹ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ እንግዶችን የሚመጥን መስተንግዶ ለመስጠት ሁለንተናዊ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይም ለጉባዔው እንግዶች ጥራቱን የጠበቀ፣ ቀልጣፋ እና ዘመኑን የዋጀ አስተማማኝ አገልገሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት፡፡

በሆቴሎቹ የሚሰጥ አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና የኢትዮጵያን ባህል እና እሴቶች የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ዝግትጅ መደረጉን አንስተዋል፡፡

ለጉባዔው የሚመጡ እንግዶች የኢትዮጵያን የቡና አፈላል ሥርዓት እንደሚናፍቁ አውስተው÷ ለዚህም ሆቴሎች በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንግዶች በአዲስ አበባ ቆይታቸው አይረሴ ትዝታዎችን እንዲያሳልፉም ባህላዊ ጭፈራዎችን ጨምሮ ሌሎች ኩነቶች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡

ዝግጅቶቹ የአፍሪካውያንን ባሕል እና እሴት ያማከሉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ሆቴሎች እንግዶችን ያለምንም የጸጥታ ችግር፣ የውሃ እጥረት፣ የመብራት እና የስልክ መቆራረጥ እንዲያስተናግዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መሰራቱንና ዝግጅቱ መጠናቀቁን ጠቅሰው፤ እንግዶችን በተለመደው የኢትዮጵያዊነት እንግዳ አቀባበል ሥርዓት ማስተናገድ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የህብረቱ 38ኛው የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 8 እና 9 የሚካሄድ ሲሆን፤ 46ኛው የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።

በመላኩ ገድፍ