የሀገር ውስጥ ዜና

ተቋማቱ ግምታዊ ዋጋቸው 34 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ድጋፍ ለተፈናቃዮች አደረጉ

By Tibebu Kebede

July 27, 2020

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ግምታዊ ዋጋቸው 34 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ ለተፈናቃዮች አደረጉ።

ድጋፉ በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው የፀጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለሚያሰባስበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አማካይነት የተደረገ ነው።

በስነ ስርአቱ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌውና የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ ተገኝተዋል።

ድጋፉ የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ምስር፣ ፓስታና አልባሳት መሆኑንን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡

አፈ ጉባዔ ታገሰ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ኅብረተሰቡ ከኢትዮጵያዊ እሴት ውጭ የተፈፀመውን አስነዋሪ ተግባር በማውገዝ ተጎጂዎችን ለማፅናናትና ለማቋቋም በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

አቶ ላቀ በበኩላቸው በሃገሪቱ የተከሰተውን ችግር ለማለፍ መደጋገፍና በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።