የሀገር ውስጥ ዜና

ዓይነ ሥውሩ የአገው ፈረሰኛ…

By Melaku Gedif

February 01, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ ሰውነት ይባላል፤ ዓይነ ሥውር ሲሆን የአገው ፈረሰኞች ማህበር አባልም ነው፡፡

የእንጅባራው ፈርጥ አዲስ የአገው ፈረሰኞች ማህበር ምስረታ በዓል የየዓመት ጌጥ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል፡፡ፈረሥ አሠጋገሩ፣ደግሞም ከፈረሱ ጋር ያለው መግባባት ልዩ ነው ይባልለታል።

የእሡን ከሁሉም የቀደመ “አጃይብ” የሚያሥብል ግልቢያ ለተመለከተ ምንም ነገር የውስጥ መሻት ከታከለበት ይቻላል የሚለውን ብሒል ማረጋገጫ ነው።

አዲሱ በልጅነት እድሜው ያደረበትን የፈረስ ግልቢያ ፍቅር ለማጣጣም ዓይነ ሥውር መሆኑ እንዳላገደው ይናገራል፡፡

በፈረስ ግልቢያ ጥበቡም በየዓመቱ በሚካሄደው የአገው ፈረሰኞች በዓል የፈረስ ግልቢያ ትርዒት ላይ ታዳሚዎችን ማስደመሙን ቀጥሏል፡፡

ከ80ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ክብረ በዓል ጀምሮ አዲሡ “ቼ ፈረሤ” ብሎ ሲጋልብ እሱን ማሸነፍ የማይታሠብ መሆኑን ጓደኞቹ ይመሠክሩለታል።

ልበ ብርሃኑ አዲስ በፈረስ ግልቢያ በተሳተፈባቸው ውድድሮች ሁሉ “እረትቼ እንጂ ተረትቼ አልገባም” ሲል ይናገራል፤ ከፈረስ ጋር ያለው ቁርኝነት እንደሚቀጥልም አውስቷል፡፡

በሰለሞን ይታየው