የሀገር ውስጥ ዜና

አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በዘርፉ የተጀመሩ ሥራዎችን ያጠናክራል – አቶ ጌታቸው ረዳ

By Melaku Gedif

February 01, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎችን እንደሚያጠናክር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

አዲሱን የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅ መርሐ ግብር ዛሬ በመቐለ ከተማ ተካሂዷል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በዚሁ ጊዜ÷ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ለማጎልበት የሚያግዙ ሥራዎችን ማከናወንና ሜካናይዜሽን ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፖሊሲው የክልሉን እርሻ ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት ስለሚያጠናክር ለተግባራዊነቱ ባለድርሻ አካላት የተለየ ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የፖሊሲ ምርምርና ጥናት መሪ ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ መንግስቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ለውጦችን ለማምጣት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽንን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በግብርና ዘርፍ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ እንደሆነም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡