የሀገር ውስጥ ዜና

2ኛው ዙር ዓለም አቀፍ የቁርአንና የአዛን ውድድር ተጠናቀቀ

By ዮሐንስ ደርበው

February 02, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ዙር ዓለም አቀፍ የቁርአንና የአዛን ውድድር ተጠናቀቀ፡፡

ውድድሩ የተካሄደው በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የበላይ ጠባቂነት እና በዘይድ ኢብኑ ሳቢት የቁርአን ማኅበር አዘጋጅነት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የውድድሩን መጠናቀቅ ተከትሎም በቁርአን ሂፍዝ፣ በቁርአን ቲላዋና በአዛን ዘርፍ አሸናፊዎች ታውቀዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በወንዶች በቁርአን ሂፍዝ ውድድር ሙሐመድ ፉዓድ (ከሊቢያ)፣ ዩሱፍ አሺር (ከኳታር) እና አህመድ በሺር (ከአሜሪካ) በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

እንዲሁም በሴቶች የቁርአን ሂፍዝ ውድድር ሩቅያ ሳላህ (ከየመን)፣ ነሲም ጀናዉጃ (ከአልጄሪያ) እና ቀመራ ወሊዩ መሐመድ (ከኢትዮጵያ) በቅደም ተከተል ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቅቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በአዛን ውድድር ሙሀመድሻን አቡበከር (ከኢንዶኔዢያ)፣ ኡመር ዱራን (ከቱርክ) እና አደም ጅብሪል (ከኢትዮጵያ) ከአንድ እስከ ሦስት በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በወንዶች የቁርአን ቲላዋ አሸናፊዎች ደግሞ አብዱራዛቅ አል ሸሀዊ (ከግብፅ)፣ ከራር ለይስ (ከኢራቅ) እንዲሁም አንጀድ ካምዳን (ከየመን) ናቸው፡፡

ከጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው ውድድር ላይ ከ60 በላይ ሀገራት ተሳትፈዋል መባሉን የጠቅላይ ምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ የሀገሩን ሰላም ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊጠብቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼይኽ ሐጅ ኢብራሂም በውድድሩ ላይ ባደረጉት ንግግር አሳስበዋል፡፡

ውድድሩ ለቁርአን ያለንን ክብርና ፍቅር ያየንበት ነው፤ ለቁርአን የሚሰጥ ክብርና ፍቅር ከዚህ በላይ እንዲሆንም ጥረት ልናደርግ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡