አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 199 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 1 ሺህ 146 አልሚዎች ፈቃድ መስጠቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ለፋና ዲጂታል እንደገለጸው÷ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ካሳ ከፍለው መሬት ለሚወስዱ አልሚዎች 2 ሺህ 404 ነጥብ 78 ሔክታር መሬት በሳይት ፕላን ማዘጋጀት ተችሏል፡፡
ለሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎችም 40 ሺህ 998 ሔክታር መሬት በሳይት ፕላን ማዘጋጀት መቻሉን ገልጿል፡፡
እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለ150 አልሚዎች በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ደግሞ ለ131 አልሚዎች መሬት አስተላልፌአለሁ ብሏል፡፡
103 አዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ማስገባት መቻሉን የገለጸው ቢሮው÷ በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎችም 132 ፕሮጀክቶችን በአዲስ ወደ ምርት (አገልግሎት) ማስገባት መቻሉን አመላክቷል፡፡
በዮሐንስ ደርበው