አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎትና እንቅስቃሴ ለማስረጽ 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ተናገሩ፡፡
ጉባዔው የሚፈጥረውን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እንደሚገባም ነው ምሁራኑ ያስገነዘቡት፡፡
ከኅብረቱ ዋና አጀንዳዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የጀመረችውን ፍትሐዊና አብሮ የመልማት ፍላጎት አንዱ ጉዳይ በማድረግ ማስረጽ እንደሚገባ በዋቼሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም መክረዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ደረጄ ፍቅሬ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎትና እንቅስቃሴ ለማስረጽ የኅብረቱ ጉባዔ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የጀመረችው ጉዞ ተሳስሮ አብሮ የማደግ አንዱ የኅብረቱ እሴት መሆኑን አስረድተው÷ ጉዳዩን የአፍሪካ አጀንዳ ማድረግ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጉዳዩን እንዲያጤኑት የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መከተል እና የጎንዮሽ ምክክር ማድረግ እንደሚገባም ነው ምሁራኑ ያስገነዘቡት፡፡
በወርቃፈራው ያለው