አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አስገዳጅ ደረጃ የወጣላቸው ሁሉም ምርቶች ብሔራዊ የደረጃ ምልክት መጠቀም እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ሀብቴ÷ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅትና ለብሌስ አግሮ ፉድ ኢንዱስትሪ ውክልና በመስጠት ብሔራዊ የደረጃ ምልክት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል ።
አሁን ላይ ግን ኢንስቲትዩቱ ውክልናውን በማንሳት ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ አስገዳጅ ደረጃ ለወጣላቸው ምርቶች ብሄራዊ የደረጃ ምልክት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በሀገሪቱ ለ370 ምርቶች አስገዳጅ ደረጃ መውጣቱን ጠቁመው÷እነዚህ ምርቶች ብሄራዊ የደረጃ ምልክት ካልተጠቀሙ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው አሳስበዋል ።
ብሄራዊ የደረጃ ምልክት መጠቀም የተጠቃሚዎችን ጤንነት ለመጠበቅና የምርት ባለቤቶች በተመሳሳይ ምርት ጉዳት እንዳይደርስባቸው እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ