የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ህብረት ተሳታፊ ሀገራት ቀዳሚ ልዑክ የህብረቱን ጉባዔ ዝግጅት ጎበኘ

By Mikias Ayele

February 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት ተሳታፊ ሀገራት ቀዳሚ ልዑካን ቡድን አባላት በአዲስ አበባ እየተደረገ ያለውን የህብረቱን ጉባኤ ዝግጅት ጎብኝተዋል፡፡

የቡድኑ አባላት ብሔራዊ ቤተመንግሥት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የክብር ሳሎን፣ አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር እና የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አዚዛ ገለታ (ዶ/ር)÷ ጉብኝቱ  ኢትዮጵያ ለጉባዔው እያደረገች ስላለው ዝግጅት ተሳታፊ ሀገራት በቂ መረጃ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

ለዘንድሮው የሕብረቱ ጉባዔ ኢትዮጵያ በላቀ ደረጃ ዝግጅት በማድረግ የተሳካ መስተንግዶ ለመስጠት እየሰራች መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ እንግዶች ኢትዮጵያ ስኬታማ ጉባዔን ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጓን እንደተገነዘቡ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ  መረጃ ያመላክታል፡፡