አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከስደትና ከስደት ተመላሾች ጋር በተያያዘ እያከናወነች ያለውን ጥረት እንደምትደግፍ ኔዘርላንድስ አስታወቀች፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ከኔዘርላንድስ የፍትሕና ደህነነት ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሮብ ቫን ባህሆቨ ጋር መክረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ወቅት÷ኢትዮጵያ ስደትና ከስደት ተመላሾች ጋር በተያያዘ እያከናወነች ያለውን ተግባር በሚመለከትና በቀጣይ ከኔዘርላንድስ ጋር በዘርፉ ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በተጨማሪም ተቋሙ በሪፎርም ሒደት ላይ መሆኑን እና የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማደራጀት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሮብ ቫን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ስደትና ከስደት ተመላሾችን በሚመለከት እያከናወነች ያለችውን ስራ እንደሚያደንቁ ገልፀው፥ሀገራቸው በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ሁለቱ አካላት በተለይም በአቅም ግንባታ ዘርፍ ላይ ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ይበልጥ ቀልጣፋ ከማድረግ አኳያ በጋራ ሊሰሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡