የሀገር ውስጥ ዜና

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ

By yeshambel Mihert

February 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የሦስተኛ ዘመን አራተኛ ዓመት ዘጠነኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር የአስተዳደሩንና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት የበጀት ዓመቱን ስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለጉባዔው እያቀረቡ ይገኛሉ።

በሪፖርታቸው በገጠርና በከተማ የአስተዳደሩ ክላስተሮች ባለፉት ስድስት ወራት በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በፖለቲካ፣ ዘላቂ ሰላምን በማስፈንና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎችን እያቀረቡ ነው።

ጉባዔው በሪፖርቱ ላይ አስተያየት በማቅረብና ጥልቅ ውይይት በማድረግ የቀረበውን ሪፖርት እንደሚያፀድቁም ይጠበቃል።

ጉባዔው በተጨማሪ የድሬዳዋ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የዳኞች ሥነ-ምግባር እና የዲሲፕሊን ክስ ሥነ-ስርዓት ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ያፀድቃል መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የድሬዳዋ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ምክር ቤቱ በመጨረሻም የተለያዩ ሹመቶችን በማፅደቅ መደበኛ ጉባዔውን ያጠናቅቃል።