አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለወንጀል መንስኤ የሆኑ አዋኪ ድርጊቶች እና ለህብረተሰቡ የደህንነት ስጋት የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ሕጋዊ የንግድ ሽፋንን ለሕገ ወጥ ተግባር በማዋል ሺሻ የማስጨስ እና ጫት የማስቃም አዋኪ ድርጊት ሲፈፀምባቸው የተገኙ የተለያዩ ሆቴሎች፣ ቪላ ቤቶች፣ የሌሊት ጭፈራ ቤቶችና ሌሎች የንግድ ተቋማት ላይ ሕጋዊ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ሕገ ወጥ ተግባሩን ሲፈፅሙ እና ሲያስፈፅሙ የተገኙ ግለሰቦችም በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝ የከተማዋ ፖሊስ ገልጿል፡፡
በዚህ መሰረትም ሰሞኑን የወንጀል መንስኤ እና የህብረተሰቡ የፀጥታ ስጋት የሆኑ አዋኪ ድርጊት በሚፈፀምባቸው ቤቶች ውስጥ የተገኙ ግለሰቦች በሚመለከተው አካል ርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቋል፡፡
በተለይም በቦሌ ክ/ከተማ ገርጂ አካባቢ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር አዋኪ ድርጊት በሚፈፀምባቸው ቤቶች ውስጥ የተገኙ ግለሰቦች በጊዜያዊነት ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ ተደርጎ ለፈፀሙት የደንብ መተላለፍ ጥፋት በገንዘብ ተቀጥተው በደረሰኝ ከከፈሉ በኋላ መሰል ድርጊት ውስጥ ድጋሚ እንዳይገኙ ተመክረውና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውን የፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡