የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮ- ጂቡቲ የባቡር መስመር የጭነት አቅሙን እያሻሻለ መሆኑ ተገለፀ

By Mikias Ayele

February 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ- ጂቡቲ የባቡር መስመር የገቢና ወጪ ጭነቶችን የማጓጓዝ አቅሙን እያጎለበተ እንደሚገኝ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ገለጹ፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷የባቡር መስመሩን አቅም ለማሻሻል ተጨማሪ ተንቀሳቃሽ የጭነት መሳሪያችን በመጨመር ወሳኝ የሆኑ ለውጦችን  በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የባቡር ጭነት አገልግሎቱን ከእንዶዴ እና አዳማ ወደ ሞጆ፤ ድሬዳዋና ሰበታ የጭነት ጣቢያዎች ማስፋፋት መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡

ብልሽት ያጋጠማቸውን ማሽነሪዎችና መሳሪያዎችን  በመጠገን  የተንቀሳቃሽ የጭነት ባቡር ቁጥሮችን ከ8 ወደ 21 እንዲሁም 892 የነበሩትን የትራንስፖርት ዋገኖች ቁጥር ወደ 935 ከፍ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም አግልገሎቱ የጭነት ምልልስ አቅሙን ማሳደጉን ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የገለጹት፡፡

የጭነት ጣቢያዎች አሰራር መሻሻሉ በጭነት ዘርፍ የተሻለ ቅልጥፍና በማምጣት የኢጥዮጵያን የትራንስፖርት አገልግሎት የእድገት ፍላጎት ለማሟላት የሚያግዝ ነውም ብለዋል፡፡