አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት በአምራች ኢንተርፕራይዞች ለ60 ሺህ 320 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠር መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታውቋል፡፡፡
የተቋሙ የሕዝብ ግንኙትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮቤል አሕመድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ የኢንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም ለማሳደግ በትኩረትና በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም ለኢንተርፕራይዞች የማምረቻ ቦታ፣ የፋይናንስና የግብዓት አቅርቦትን ከማሳካት ባለፈ የተለያዩ የሞያ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ኢንተርፕራይዞች በተኪ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በግማሽ ዓመቱ በክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች 1 ሺህ 527 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም መቻሉን አንስተዋል፡፡
በሌላ ከኩል 5 ሺህ 732 ነባር ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር ታቅዶ 7 ሺህ 446 አምራች ኢንተርፕራይዞችን ማጠናከር ተችሏል ነው ያሉት፡፡
አዲስ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋምና በማጠናከርም ለ60 ሺህ 320 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የደረጃ ሽግግርን በተመለከተ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ 897 እንዲሁም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ደግሞ 13 ኢንተርፕራይዞችን መሸጋገራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ