አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ዴንማርክ ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መስፈን የምታደርገውን ድጋፍ አደነቁ።
ዋና ጸሐፊው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር እንዲሁም የሀገሪቱ የኢጋድ ተወካይ መልዕክተኛ ሱን ክሮግስትረፕ የሹመት ደብዳቤ መቀበላቸውን ገልጸዋል።
በወቅቱ ባደረጉት ውይይት በኢጋድ እና በዴንማርክ መንግስት ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የትብብር መስኮች ዙሪያ መክረዋል።
በተለይም በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም ግጭት አፈታት ዙሪያ በትብብር መስራት ስለሚቻልበት ሁኔታ በስፋት ተወያይተዋል።
የዴንማርክ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ለሚያደርገው ያልተቆጠበ ድጋፍም ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡