የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ተጠናቀቀ

By Feven Bishaw

February 13, 2025

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።

“የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች ተሳትፈዋል።

ምክር ቤቱ ለሁለት ቀን ባካሄደው ስብስባ በተለያዩ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በህብረቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ምክር ቤቱ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንር ስር የሚገኙ የስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ ተካሄዷል።

ኢትዮጵያ ትናንት የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት ሆና ተመርጣለች።

የስራ አስፈጻሚው አካል የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚከናወነው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን አፅድቋል።

የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የማካካሻ ፍትህ፣ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ለማግኘት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ አህጉራዊ ሰላምና ደህንነት ውይይት ከተደረገባቸው ዋንኛ አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

እንዲሁም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አፈጻጸምና አህጉራዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር፣ ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ ስርዓተ ጾታና ወጣቶችን ማብቃት እንዲሁም የተቋማትና አደረጃጀቶች ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።