የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ሪፎርም መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ እየተከናወነ ነው – ሙሳ ፋቂ ማሃማት

By Feven Bishaw

February 15, 2025

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ሪፎርም መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት ገለጹ፡፡

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ “የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ በሕብረቱ አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የሞሪታኒያ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ሞሃመድ ኡልድ ጋዙዋኒ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ፣ የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማያ ሞተሊ፣ የፍልስጤም መሪ ማህሙድ አባስ እና የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በአፍሪካ ባለፉት 10 ዓመታት በተለይም ግጭትና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የመንግስትና የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍሰት በእጅጉ ሲፈትን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተከሰተው ጦርነት የግብርና ምርት አቅርቦትን በመቀነስ በአፍሪካውያን ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አፍሪካ ባለፉት አስርት ዓመታት በእነዚህ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ችግሮች ውስጥም ሆና ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

ብሉ ኢኮኖሚ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የትምህርት ተደራሽነት፣ ሰብዓዊ ድጋፍን ማዳረስ እንዲሁም ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታተ የተደረገው ጥረት መልካም እንደነበር አንስተዋል፡፡

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አንዱ የስኬት ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ የመንግስታቱ ድረጅት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ላለው አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው ግጭት አሳሳቢ መሆኑን አንስተው፤ በሊቢያ ተፃራሪ ሀይሎች መካከል ትናንት የተፈረመውን ስምምነት በመልካምነት ጠቅሰዋል፡፡

የአጀንዳ 2063 የመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት አፍሪካ የምትፈልገውን ለመሆን ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ግንባታ ማካሄድ እንዳለባትም አመላካች መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ተቋም፣ የሰላምና ደህንነት ምክር ቤት እና ሌሎችም አፍሪካው ተቋማት ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።