አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መንገድ ሳይዘጋ ሰሞኑን ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሠ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ከጉባዔው ቀደም ብሎ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መጠነ-ሰፊ የዝግጅት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በቂ ዝግጅት መደረጉን ተከትሎም ቀደም ሲል ይደረግ እንደነበረው መሪዎች ከማረፊያቸው ወደ መሰብሰቢያ ቦታ እንዲሁም ከመሰብሰቢያ ቦታ ወደ ማረፊያቸው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት መንገድ አልተዘጋም፡፡
እንግዶች ሲያልፉ ሕብረተሰቡ እና አሽከርካሪዎች የመንገዱን ዳር በመያዝ በአክብሮት ማሳለፋቸው የሚደነቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በመሪዎቹ በኩል የተሰጡ አስተያየቶች የሥራችንን ስኬታማነት አረጋግጠዋል ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ ለቀጣይ አኅጉራዊ እና ሀገራዊ ጉባዔዎች ተሞክሮ የሆነ ሥራ መሠራቱን ጠቁመው÷ በመደበኛ ሥራ ጭምር ተካትተው ሊከናወኑ የሚችሉ ልምዶች ተገኝተውበታል ነው ያሉት፡፡
ጉባዔው የተሳካ እንዲሆን የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ በርካታ የጸጥታ አካላት እና የትራፊክ ፖሊሶችን ጨምሮ የሕብረተሰቡ አደረጃጀቶች አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሕብረተሰቡን እና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ ሁሌም ስኬታማ መሆኑን የተረዳንበት ጉባዔ ነበር ያሉት ኮማንደር ማርቆስ፤ ለጸጥታ አካላት እና ለመዲናዋ ነዋሪዎች ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ መንገድን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በከፍተኛ ደረጃ መሻሻላቸው በጉባኤው ወቅት እንግዶችን ለማስተናገድና የትራፊክ ፍሰቱን ለማቀላጠፍ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉም ተጠቁሟል።
በዮሐንስ ደርበው