አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግስታት የሰላም ግንባታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሒደት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው÷የኢትዮጵያ ሕዝብ ምክክሩን በቅርበት እየተከታተለውና እየደገፈው እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምታደርግ የገለጹት ሚኒስትሩ÷ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸው በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱንም አስረድተዋል፡፡
ሮዝማሪ ዲካርሎ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥም ሆነ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለምታደርገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ጌደዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር (ዶ/ር) ጋር በአፍሪካ ቀንድ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡