አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድግ ፖሊሲ በመተግበር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ በዘላቂነት ራስን ለመቻል እየሰራች መሆኗን ገለጸች፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫውም ፥ አፍሪካ በዕርዳታ ላይ ጥገኛ ተደርጋ በዓለም የተሳለችበትን የትርክት ምስል ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል ቆራጥ ርምጃዎችን በመውሰድ ለመቀልበስ እየሰራች መሆኗ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ሥድስት ዓመታት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ፖሊሲዎችን ወደተግባር በመቀየሩ የምግብ ዋስትናን ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ራሷን እንድትችል ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
እነዚህ ጥረቶች ኢትዮጵያን ከጥገኝነት ለማላቀቅ እና ዘላቂ ልማቷን ለማጎልበት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቁ ናቸው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገራዊ እድገትን ለማዳከምና የልማት ጥረቶችን በተለይም በግብርናው ዘርፍ ለማጣጣል የሚስተዋሉ የውጭ ጥረቶች እንዳሉ ያነሳው መግለጫው ሆኖም ግን ቁርጠኝነታችን ለሀገራችን እና ለህዝባችን ህልውና አስፈላጊ ስለሆነ አይናወጥም ሲል አስገንዝቧል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ በዋነኝነት በፈረንጆች 2022/23 15 ነጥብ 1 ሚሊየን ቶን የስንዴ ምርት ያመረተች ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ በመኅር ወቅት 10 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን እንዲሁም 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ስንዴ በበጋ ወቅት የተመረተ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በ2023/24 ደግሞ 23 ሚሊየን ቶን ስንዴ የተመረተ ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ 12 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን በመኅር እንዲሁም 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን በመስኖ ማምረቷ ተጠቅሷል፡፡
እነዚህ የቁጥር መረጃዎችም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ላይ እያስመዘገበች ያለችውን ከፍተኛ እድገት በማሳየት በምግብ ራሷን ለመቻል ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነውም ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርት በቂ ስላልነበር ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ የስንዴ ምርቶች በዓመት 1 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ስታደርግ መቆየቷን መግለጫው አስታውሷል፡፡
ሆኖም ግን ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያ የስንዴ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ ማቆሟንም አውስቷል፡፡
በዚህም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የምግብ እራስን መቻል ሀገራዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ወሳኝ ርምጃ መሆኑም ተነስቷል፡፡
በዚህም በምግብ ራስን መቻል በሌሎች ላይ ጥገኛ አለመሆንን እና በአህጉሪቱ ዘላቂ እድገት ለማምጣት መንገድ የሚከፍት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ጉዞው አድካሚና ፈታኝ መሆኑን ያነሳው መግለጫው ፥ የኢትዮጵያ የግብርና ለውጥ ራስን ለመቻል ለሚጥሩ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ እንደሆነም ነው የተነሳው፡፡
ዘላቂ የግብርና እና ሌሎች መፍትሄዎችን በማስቀደም ኢትዮጵያ አፍሪካ ራሷን የመመገብ አቅም እንዳላት እና ለመጪው ትውልድ ብልጽግናን እያሳየች ነው ፤ ይህም ኢትዮጵያ የምትኮራበት ጉዞዋ ነው ብሏል መግለጫው፡፡