አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ እና መጠን የትራፊክ አደጋዎች በርካታ ጉዳት ሲያደርሱ ይስተዋላል፡፡
ኢትዮጵያ በቁጥር አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን ይዛ ከፍተኛ አደጋ ከሚያስተናግዱ ሀገራት ተርታ እንደምትገኝ የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ትምህርትና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዮሐንስ ለማ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
አደጋ ከሚያስከትሉ መንስዔዎች መካከልም÷ የባለንብረቶች ቸልተኝነት፣ ከተፈቀደው መጠን በላይ መጫን፣ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎችን ለሕዝብ ማጓጓዣ መጠቀም፣ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ክፍተት፣ የተሽከርካሪ ቴክኒካል ችግር እና የቁጥጥር መላላት ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በማሰልጠኛ ተቋማት ላይ በተደረጉ ጥናቶች መሠረት ስልጠናውን በአግባቡ ሳይከታተሉ መንጃ ፈቃድ የመውሰድ እና ሐሰተኛ የመንጃ ፈቃድ ማስረጃ በመያዝ የማሽከርከር ሁኔታዎች እንዳሉ ተደርሶበታል ነው ያሉት፡፡
ይህን ተከትሎም በተከናወነ ሥራ ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ ፈቃድ እስከ መሠረዝ የደረሰ ርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡
በመሆኑም እንደ ተቋም የተሽከርካሪ አደጋን መከላከል እና አፋጣኝ የሕክምና አገልግሎት ማቅረብን መሠረት ያደረገ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ያመላከቱት፡፡
አሁን ላይ የመንገድ ደኅንነት በሥርዓተ-ትምህርቱ መካተቱትን እና በማሰልጠኛ ተቋማት ያለውን የሥልጠና ሂደት ከሥር ከሥር የመከታተል ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ከተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ ጋር የተያያዙ የቁጥጥር ሥራዎች እና የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ከፍተኛ አደጋ እያስከተሉ ያሉት በአብዛኛው የንግድ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን በመግለጽ፤ ባለንብረቶች እና አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል፡፡
በአጠቃላይ ከሕጋዊ አሠራርና ሂደት ውጭ ያሉ መንጃ ፈቃዶች እና ቦሎዎች አደጋ እያስከተሉ መሆኑን በመረዳት ድርጊቱ ሲያጋጥም ሕብረተሰቡ ጥቆማ በመሥጠት ተባባሪ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው