የሀገር ውስጥ ዜና

ስፑትኒክ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፈተ

By ዮሐንስ ደርበው

February 19, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው የዜና እና ሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ መክፈቱን ይፋ አደረገ።

የአዲስ አበባው “ስፑትኒክ አፍሪካ” የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብር የኤዲቶሪያል ፖሊሲ እና ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን የያዘ አደረጃጀት እንዳለውም ተገልጿል።

ስፑትኒክ አፍሪካ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ድምጽ በመሆን እድገትና ብልጽግናቸውን ለማሳካት አጋዥ ሚና እንደሚወጣም ተጠቁሟል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን ፌዴራል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቫለንቲና ማትቪዬንኮ እንዳሉት፤ ስፑትኒክ አፍሪካ የአፍሪካውያን ጥቅምና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው።

የስፑትኒክ አፍሪካን ቢሮ መከፈት ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር የማጠናከር ግብ ለማሳካት ወሳኝ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሩሲያና ኢትዮጵያ በባሕል፣ በእምነትና በዓለም አቀፍ ትብብር ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ስፑትኒክ አፍሪካ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ትክክለኛ መረጃ በማውጣት አንዱ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ነው ያሉት።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፤ ስፑትኒክ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ተደራሽ በመሆኑ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታ ለዓለም በማስተዋወቅ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።

የስፑትኒክ አፍሪካ በአዲስ አበባ መከፈቱ የሁለቱን ሀገራት ትብብር የሚያሳይና የሚያጠናክር መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ሁሉን አቀፍ ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ተጨማሪ የትብብር መንገድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሚዲያው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡