የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

By ዮሐንስ ደርበው

February 19, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት ከሩሲያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መንግሥታት መካከል የመጀመሪያው የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ለሦስት ዓመታት የሚያገለግል ሁለተኛው ፍኖተ ካርታ ዛሬ ተፈርሟል።

ሀገራቱ በኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ በባሕል ልውውጥ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ሽግግር፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በግብርና በንግድ ልውውጥ እና በመሰረተ-ልማት ዝርጋታ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ምክክር አድርገዋል፡፡

የምክክሩ ዓላማም የኢትዮጵያና የሩሲያን የሁለትዮሽ ግንኙነት በይበልጥ በማሳደግ የጋራ ስምምነቶችን ለመፍጠር መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር የምትጋራውን ዘመናት ያስቆጠረ እና ታሪካዊ ግንኙነት ከፍ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት ፍሬማ መሆኑን በኢትዮጵያ በኩል የኢትዮ-ሩሲያ የበይነ-መንግስታቱ የጋራ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የምናከናውናቸው የአጋር ስምምነቶች የዛሬውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ከማንሳት ባለፈ፤ ለቀጣይ ትውልዶች ጸንቶ የሚዘልቅና የሚለመልም አጋርነት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

ከሩሲያ በኩል የበይነ-መንግስታቱ የጋራ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ ማክዚም ረሽቲንኮቭ በበኩላቸው፤ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት እያከናወነቻቸው ያሉ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን በይበልጥ የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም በንግድ፣ ጤና፣ በባንክ ሥርዓት፣ በኢነርጂ፣ በቴክኖሎጂ፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በቱሪዝምና ንግድ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት እንደምትፈልግ ተናግረዋል፡፡