የሀገር ውስጥ ዜና

ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ለማስገባት ሲባል የመንግሥትን አገልግሎት በገንዘብ መግዛት አይቻልም – ሚኒስቴሩ

By ዮሐንስ ደርበው

February 21, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እጅ ጠምዝዞ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የመንግሥትን አገልግሎት በገንዘብ ለመግዛት መሞከር ፈጽሞ እንደማይቻል የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስጠነቀቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት፤  የምርት ጥራት በደረጃ መስፈርት ይወሰናል እንጂ በገንዘብ አይገዛም ብሏል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 13 የምርት አይነቶች ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባታቸው አስቀድመው በመነሻ ሀገራት በ ‘Cotecna እና Bureau Veritas’ በተባሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላቸው የኢንስፔክሽን ተቋማት የቅድመ ምርት ጭነት ፍተሻ ምስክር ወረቀት ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

በተለይም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ አስመጪዎች ምርቶቹን በመነሻ ሀገራት ጥራታቸውን ለማረጋገጥ አስፈትሸው የቅድመ ጭነት ኢንስፔክሽን ፍተሻ ምስክር ወረቀት በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡበት አሠራር ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብሏል።

ይሁን እንጂ ይህንን አሠራር በመጣስ አነዚህን ምርቶች ከመነሻ ሀገር ሳይሆን ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት መሞከር የኅብረተሰብን ደህንነትና ጥቅም ይጎዳል፤ አካባቢንም ለብክለት ያጋልጣል፤ የሀገርን ኢኮኖሚም ይጎዳል ነው ያለው ሚኒስቴሩ በመልዕክቱ።

በዚህ ረገድ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ የሚገኙት ከመነሻ ሀገራት የቅድመ ጭነት ኢንስፔክሽን ሳያከናውኑ የሶስተኛ ወገን የምርት ጥራት ፍተሻ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ሳይዙ በሀገር ውስጥ በጉምሩክ ጣቢያ ከደረሱ በኋላ የጥራት ፍተሻ ወረቀት ተሰጥቷቸው እንዲገባ የሚፈልጉ አካላት ናቸው ሲልም ገልጿል፡፡

እጅ ጠምዝዞ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የመንግሥትን አገልግሎት በገንዘብ ለመግዛት መሞከር ፈጽሞ የማይቻል መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡

ማንኛውም አስመጪ ሀገርንና ሕዝብን ከሚጎዱ ሕገ ወጥ ድርጊቶች እንዲቆጠብና የተቀመጠውን የአሠራር ሥርዓት ተከትሎ እንዲሠራ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡