የሀገር ውስጥ ዜና

የብልጽግና እና ኤኬ ፓርቲ ግንኙነት ተጠናክሮ ቀጥሏል- አቶ አደም ፋራህ

By ዮሐንስ ደርበው

February 24, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብልፅግና ፓርቲ እና በቱርኩ ኤኬ ፓርቲዎች መካከል ያለው ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

ኤኬ ፓርቲ ባካሄደው 8ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በመገኘት በብልፅግና ፓርቲ እና በኤኬ ፓርቲ መካከል ባሳለፍነው ወር በጋራ ለመሥራት የተፈራረምነው የመግባቢያ ሠነድ ተግባራዊነት እንዲፀና አንድ ርምጃ ወደፊት መጓዝ ችለናል ብለዋል አቶ አደም፡፡

ኢትዮጵያ እና ቱርክ በርካታ ዘመናትን ባስቆጠረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው፤ በመንግስት ለመንግስት እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ደረጃ የተፈጠሩ ግንኙነቶችንና የተገኙ ውጤቶችን በብልፅግና እና በኤኬ ፓርቲ ስምምነት የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን በማጠናከር በቀጣይ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እመርታዎችን ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ችለናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በተለይም በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ እና በቀጣናዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ያለው ትብብር እና እየተገኙ ያሉ እመርታዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በፓርቲዎቹ መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፈጠሩን ነው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ያሰፈሩት፡፡

ኤኬ ፓርቲ ባካሄደው 8ኛ ጉባዔ ላይ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶኻን የፓርቲው ሊቀ-መንበር ሆነው በመመረጣቸው እንዲሁም ሌሎች በጉባዔው ለፓርቲ አመራርነት ለተመረጡ በሙሉ በብልፅግና ፓርቲ ስም የእንኳን ደስ አላች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡