አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪዝም ሃብት የሚመጥን የማስተዋወቅ ሥራ ሊሰራ ይገባል ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚህ ወቅት÷ በግማሽ ዓመቱ በቱሪዝም ዘርፍ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው÷ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብቶች የማስተዋወቅ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ሁነቶች ማስተናገዷን ያስታወሱት ሚኒስትሯ÷ ይህም የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ እድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ሰጪዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
በቀጣይም በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን እምቅ የቱሪስት ሃብት የሚመጥን የማስተዋወቅ ሥራ ማከናወነን እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡