የሀገር ውስጥ ዜና

ለላቀ አኅጉራዊ ዕድገት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራን ማፋጠን ይገባል ተባለ

By ዮሐንስ ደርበው

February 26, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ አኅጉር የላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራን ማፋጠን እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስቴሩ ከኤክስቴንሲያ ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት የሚቆይ የአፍሪካ ዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚመክር የ2025 ፈጣን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉባዔ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡

ጉባዔው በአፍሪካ ፈጣን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራን በማሳለጥ የላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ያለመ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ሚኒስትሩ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግርም፤ የፓን አፍሪካን የፖሊሲ አውጪዎች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ባለሀብቶች በአፍሪካ የዲጂታል ለውጥ ለማፋጠን በቅንጅት መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡

የተግባር ጊዜ አሁን ነው፤ በመላው አኅጉር፣ ዲጂታላይዜሽን ኢኮኖሚዎችን ለመገንባት፣ አዳዲስ ዕድሎችን በመክፈት እና አፍሪካ በዓለም አቀፍ ገበያ ያላትን አቋም ለማሳደግ በትጋት መሠራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የዲጂታል አገልግሎቶች እና በአይሲቲ የሚመሩ ኢንዱስትሪዎች ያላቸውን ዐቅም ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ እምቅ ዐቅምን ለመገንዘብ እና ሁሉን አቀፍ እድገት ለማምጣት ትብብርን፣ ፈጠራንና ቆራጥ ርምጃን እንደሚጠይቅም አብራርተዋል፡፡

የኤክስቴንቲያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታሪቅ ማሊክ በበኩላቸው፤ ለአኅጉሪቱ የተፋጠነ የዲጂታል እድገት አዳዲስ ዕድሎችን በማጉላት፣ በቁልፍ ውሳኔ ሰጪዎች፣ በዘርፉ መሪዎች እና ባለሀብቶች መካከል ትስስርን ለማጎልበት ብሎም ፈጠራን ለማስፋፋት ጉባዔው ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

ፈጣን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራን በማሳለጥ የአፍሪካን የወደፊት ዲጂታል ኢኮኖሚን በቅንጅትና በትብብር በመገንባት የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንደሚሠራ በጉባዔው ላይ ተገልጿል።