የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ግዳጁን በብቃት እየተወጣ መሆኑ ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

February 26, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ግዳጁን በላቀ ብቃት እየተወጣ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ኃይል አዛዥ ሌ/ጄኔራል ምሃን ሰበርማኒያን ገለጹ።

በደቡብ ሱዳን ለሚገኘው የ19ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል የሜዳሊያ ማልበስ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

ሌተናል ጄኔራሉ በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ጠንካራ፣ ለችግሮች የማይንበረክና የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡

ሠራዊቱ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ የሚያበረክተው ሁለንተናዊ ድጋፍም ሕዝባዊነቱን የሚያረጋግጥ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት በየትኛውም የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሰማርቶ ግዳጁን በላቀ ሁኔታ የሚፈጸም መሆኑንም በደቡብ ሱዳን ሥምሪቱ አረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል ዓለሙ ኪንኪና በበኩላቸው፤ አባላቱ ውስብሰብ ግዳጅ ተወጥተው ለሜዳሊያ ቀን በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡