የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 1 ሺህ 244 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ተለቀቁ

By Tibebu Kebede

July 30, 2020

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል 1 ሺህ 244 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ መለቀቃቸውን የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የአቃቤ ሕጉ ህዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አለምሸት ምህረቴ  እንደገለጹት የህግ ታራሚዎቹ በይቅርታ የተለቀቁት ከሐምሌ 21/2012 ዓ.ም ጀምሮ ነው።

ይቅርታ የተደረላቸውም በመደበኛው የይቅርታ አዋጅ ቁጥር 136/1998 መሰረት እና በልዩ ይቅርታ ቦርድ ጉዳያቸው ተጣርቶ የቀረቡ ናቸው ብለዋል።

የዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከልም ዕድሜያቸው የገፋ፣ የጤና ችግር ያለባቸው፣ አንድ ሶስተኛውን እስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁና የባህሪ ለውጥ ያመጡ ይገኙበታል።

በይቅርታ ከተለቀቁት ውስጥ 22 ሴቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በሙስና ፣ በጠለፋና አስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈረደባቸው በይቅርታው አለመካተታቸውን ነው ኃላፊው ያሰረዱት።

ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ የበደሉትን ህዝብ በልማት ለመካስ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ደግሞ የክልሉ ይቅርታ ቦርድ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ አምባው አስረስ ናቸው።

ህብረተሰቡም በጥፋታቸው የተፀፀቱና ታርመው የተለቀቁ መሆኑን ተገንዝቦ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሊደግፋቸውና ሊያግዛቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም መንግስት በልዩ ሁኔታ ባደረገው ይቅርታ ከ7 ሺህ የሚበልጡ የህግ ታራሚዎች እንዲለቀቁ መደረጉ እንደሚታወቅ ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።