አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ በ2ኛ መደበኛ ጉባዔው ያሳላፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በውጤታማነት ተፈፅመው ለሀገር ተገቢውን ፋይዳ እንዲያስገኙ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ አተኩረው በ24 ከተሞች የተካሄዱ ውይይቶች በስኬት ተጠናቅቀዋል ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኮቹም 33 ሺህ 766 የልዩ ልዩ ማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች መሳተፋቸውን አቶ አደም በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
መድረኮቹ በታቀደው መሰረት እንዲፈፀሙና ተገቢው መግባባት እንዲፈጠርባቸው አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በፓርቲያችን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የተወሰኑት ውሳኔዎችና የተቀመጡት አቅጣጫዎች፤ የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነትና ዘላቂነትን ለማረጋጋገጥ፣ ዘላቂ የሆነ አዎንታዊ ሰላም ለማስፈን፣ የማህበራዊ ልማት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈን እና የዜጎች ክብርና ብሔራዊ ጥቅማችንን በተሻለ መልኩ የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ለማስመዝገብ የሚያስችሉ መሆናቸውን ሕዝቡ አረጋግጧል ብለዋል።
ለተፈፃሚነታቸውም የድርሻውን ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት ገልጿል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት ያስመዘገብናቸውን ዘርፈ ብዙ ስኬቶችንም ሆነ በቀጣይ መታረም አለባቸው ብሎ የሚያስባቸውን ጉዳዮች በልካቸው አንስቷል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በተለይም ሕዝቡ ትኩረት እንድንሰጣቸው ያቀረባቸው፤ የሰላም፣ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመሰረተ ልማት እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች፤ የሕዝቡን ተሳትፎ፣ የየአከባቢውን ፀጋ አጠቃቀም እና የመንግስትን የመፈፀም ብቃት ይበልጥ በማሳደግ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ፓርቲያችን በቁርጠኝነት ይሠራል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
ሕዝቡ እስከ አሁን ላስመዘገብናቸው ስኬቶች ሁሉ ከጎናችን በመሆን ላደረገልን ድጋፍም እናመሠግናለን ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም የጉባዔያችን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች በውጤታማነት ተፈፅመው ለሕዝባችንና ለሀገራችን ተገቢውን ፋይዳ ያስገኙ ዘንድ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አደራ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።