የሀገር ውስጥ ዜና

ለሽብር ተግባር መሰናዳት በሚል ክስ የቀረበባቸው ግለሰቦች ጥፋተኛ ተባሉ

By ዮሐንስ ደርበው

February 26, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሽብር ወንጀል መሰናዳት የወንጀል ክስ የቀረበባቸው 13 ግለሰቦች ጥፋተኛ ተባሉ፡፡

የግራ ቀኝ ማስረጃ መርምሮና አመዛዝኖ በ13 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ፤ የሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥት ሥርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በነመላክ ምሳሌ መዝገብ 20 ተከሳሾች ላይ  የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማሳካት በአካል በመገናኘት በመደራጀትና በመወያየት እንዲሁም በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም በዋትስአፕ በበይነ መረብ መገናኛ ዘዴ ላይ ዕቁብ የሚል ስም የተሰጠው መወያያ በመክፈት በጋራ በቡድን በመወያየት፣ የአማራ ብልፅግና፣ ህወሓትና የኦሮሞ ብልፅግና ጠላቶቻችን ስለሆኑ በኃይል ርምጃ መጥፋት አለባቸው የሚል ስምምነት በማድረግ፣ 5ቱ የአማራ አናብስቶች ንቅናቄ የተባለ ህቡዕ ድርጅት በመመስረት፣ ለድርጅቱ ፋይናንስ ማፈላለግ እንዲሁም የኃይል ጥቃት የሚጀመርበት ስፍራን በመምረጥ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም መሰናዳት (ዝግጅት) ማድረግ በሚል ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም የሽብር ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

በክስ ዝርዝሩ ላይም በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝባዊ አመፅ ለማስነሳት በመዘጋጀት፣ በሕዝባዊ አመፁ ወደ ቤተ መንግስት አቅጣጫ በሚታለፍበት አካባቢ ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ነዳጅ ማደያዎች እና የመንግስት ተቋማትን በማቃጠል ጉዳት እንዲደርስ እና በዚህም መንግስት መከላከል እንዳይችል አቅጣጫ በማስቀመጥ መስማማት እና በአጠቃላይ ለሽብር ተግባር መዘጋጀት የሚሉ ጭብጦች ተካትተዋል።

ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ  ከቀኑ 8 ሠዓት አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ መተባበር ሕንጻ 4ኛ ፎቅ ላይ የህቡዕ አደረጃጀት አባላትና አመራሮች ሕዝባዊ አመፅ ማስነሳትን መሰረት ያደረገ ስብሰባ በማካሄድ፣ የውኃ ልክ፣ አሸዋ፣ ሲሚንቶ፣ ግንበኛ የሚል መጠሪያ ኮድ በመሰጣጠት፣ ገንዘብ ማሰባሰብ፣ የጦር መሳሪያ እና ለወታደራዊ ምግብ ግዢ ለማዋል መዘጋጀት፣ ሕዝቡን ለማሸበርና መንግስትን ለማስገደድ በማሰብ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም መሰናዳት (ዝግጅት) ማድረግ የሚሉ ነጥቦችንና የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦ ነበር።

ይህ የክስ ዝርዝር በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾቹ  ዋስትና እንዲፈቀድላቸው በጠበቆቻቸው አማካኝነት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፤ ዐቃቤ ሕግ ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም በማለት ክርክር ተደርጓል።

የግራ ቀኝ ክርክሮችን የመረመረው ፍርድ ቤትም፤ 19 ተከሳሾች ላይ ከቀረበባቸው የሽብር ክስ ውስብስብነት አንጻር ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም የሚለውን ግምት በመያዝ የዋስትና ጥያቄያቸውን በሙሉ ድምጽ ውድቅ አርጓል።

በሌላ በኩል በዚሁ መዝገብ ቅድስት የተባለች 17ኛ ተከሳሽን በሚመለከት እራሳቸውን ለመንከባከብ አቅም የሌላቸው የአራት ልጆች እናት በመሆኗ፣ የሕጻናትን የቤተሰብ እንክብካቤ የማግኘት ሕገ መንግስታዊ የመብት ድንጋጌዎችን ታሳቢ በማድረግ እና ተከሳሿ የዋስትና ግዴታዋን አክብራ ልትቀርብ ትችላለች በሚል ፍርድ ቤቱ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንድትፈታ በሙሉ ድምፅ ብይን ሰጥቷል።

ከዚህ በኋላም ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው፤ በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል መሰረትም የዐቃቤ ሕግ ምስክር ቃልና የሰነድ ማስረጃን ፍርድ ቤቱ ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ስድስት ማለትም፤ በክስ መዝገቡ የተጠቀሱ 2ኛ፣ 7ኛ፣ 11ኛ፣ 15ኛ፣ 18ኛ እና 19ኛ ተከሳሾች ላይ በቀረበው ክስ የተጠቀሰ የወንጀል ድርጊትን ስለመፈጸማቸው የሚያስረዳ ማስረጃ በበቂ ሁኔታ በዐቃቤ ሕግ አለመቅረቡን ጠቅሶ በነጻ አሰናብቷቸዋል።

ሌሎቹ በክስ መዝገቡ የተካተቱ 14 ተከሳሾች ደግሞ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ነበር፡፡

ከዚህም በኋላም ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ የተባሉ 14 ተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ በተለያዩ ቀናት ተመልክቶና ከዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ጋር አመዛዝኖ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

በዚህም ከ14 ተከሳሾች መካከል 5ኛ ተከሳሽን ብቻ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበሉን ጠቅሶ፤ በነጻ ያሰናበተው ሲሆን፤ ቀሪ ተከሳሾችን ደግሞ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ 4ኛ እና 14 ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት በአንደኛው ክስ ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን፤ በ2ኛው ክስ ማለትም የጦር መሳሪያ መያዝ ወንጀል ክስ ነጻ ተብለዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅ ለየካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ