የሀገር ውስጥ ዜና

ቶዮ ሶላር በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሙከራ ምርት ማምረት ጀመረ

By Melaku Gedif

February 27, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በ60 ሚሊየን ዶላር የተለያዩ ሶላር ፓኔሎችን ለማምረት የገባው የጃፓኑ ቶዮ ሶላር ኩባንያ የማሽን ተከላ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የሙከራ ምርት ማምረት ጀምሯል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ÷ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የሙከራ ምርት በማምረት ላይ የሚገኘውን የቶዮ ሶላር ኩባንያን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው በዚህ ወቅት ኩባንያው በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሒደት እንዲገባ ኮርፖሬሸኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ቶዮ ሶላር የግንባታ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ አጠናቅቆ የፊታችን መጋቢት አጋማሽ ላይ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሒደት እንደሚገባ የኩባንያው አመራሮች ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው በተያዘው በጀት ዓመት በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥራ ለመጀመር ከኮርፖሬሽኑ ጋር ተፈራርሞ ወደ ስራ የገባ ሲሆን÷ ምርቶቹንም ወደ መካከለኛው ምስራቅ፣ ህንድ እና አሜሪካ እንደሚልክ ተጠቁሟል፡፡

ቶዮ ሶላር ኩባንያ በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሶስት ሄክታር የለማ መሬት እና የማምረቻ ሼድ ተረክቦ ስራ መጀመሩን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

ኩባንያው በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሒደት ሲገባም ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ቋሚ የሥራ እድል እንደሚፈጥር ነው የተገለጸው፡፡