የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ብሪታኒያ ሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ምክክር እየተካሄደ ነው

By Mikias Ayele

February 27, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያና ብሪታኒያ የሁለትዮሽ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ በፈተናዎች የማይበገር ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።

ኢትዮጵያና ብሪታኒያ በፅናት፣ በመከባበር እና በጋራ እድገት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት አሁን ላይ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ግንኙነታቸውም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም የውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት መረጃ አመላክቷል፡፡