የሀገር ውስጥ ዜና

የዓድዋ ድል ብሔራዊ አንድነት እንዲፈጠር አድርጓል – ምሁራን

By ዮሐንስ ደርበው

February 28, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመቀየርና ከማጠናከር ባሻገር ብሔራዊ አንድነት እንዲፈጠር ማስቻሉን የፖለቲካ ሣይንስ ምሁራን ገለጹ፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከሎችን እንድትከፍት፣ ድንበሮቿም እንዲለዩና ዕውቅና እንድታገኝ ማድረጉን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪው ኢያሱ ኃይለ ሚካኤል ገልጸዋል፡፡

ዓድዋ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበረና ያስጠበቀ ታሪካዊ ሁነት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፖለቲካ ሣይንስ መምህር ቻን ዮም (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሴኔሳ ደምሴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዓድዋ ላይ ባስመዘገበችው ድል ምክንያት በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁሮችን የምትወክል ሀገር ናት ብለዋል፡፡

ምሁራኑ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከዓድዋ አንድነትን፣ መደማመጥንና መተማመንን መማር እንደሚገባ መክረዋል፡፡

የዓድዋ ድል ቅኝ ግዛት ተቀባይነት የሌለው ሥርዓት መሆኑን ያረጋገጠ እና ማሸነፍ እንደሚቻልም ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በየሻምበል ምኅረት