የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ሶማሊያ ግንኙነት ዳግም እየተጠናከረ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By Mikias Ayele

February 28, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ግንኙነት ዳግም እየተጠናከረ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም÷ ከሶማሊያ ጋር ያለንን ግንኙነት በአዲስ መንፈስ ለማጠናከር የተሰራው ሥራ ውጤታማ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሊያ ሞቃዲሾ ጉብኝት ማድረጋቸው የግንኙነቱ መሻሻል እና በአዲስ መንገድ መጓዝ መጀመሩ ሁነኛ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ ግንኙነቱ በአዲስ መንገድ መጓዝ መጀመሩ በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ልማት እጣፋንታቸው የተሳሰረ እና የሶማሊያ መረጋጋት የኢትዮጵያ መረጋጋት መሆኑን ቃል አቀባዩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶች ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሠላም ማስከበርና ማረጋጋት ተልዕኮ እንደምትሳተፍ አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ሀገራት በደረሱባቸው ስምምነቶች መሠረት ሽብርተኝነትን በጋራ በመፋለም በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኀንነት ላይ ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተለያዩ አካባቢዎች በእንግልትና ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ የሚደረገው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

በዚህ መሰረትም በማይናማር ታግተው የነበሩ 246 ዜጎችን በቀጣይ ሳምንት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

በማይናማር በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለማስወጣት በቶኪዮ እና በኒውዴሊ ባሉ ኤምባሲዎች በኩል ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ 246 ኢትዮጵያዊያን ከማይናማር ወጥተው ወደ ታይላንድ መድረሳቸውን ጠቅሰው÷ እነሱን ለመርዳትና የማጣራት ሥራ ለመሥራት በነገው ዕለት አንድ ቡድን ወደ ስፍራው እንደሚያቀና አመላክተዋል።

በተመሳሳይ በመካከለኛው ምስራቅ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለማስወጣት የሚደረገው ጥረት ቀጣይነት እንዳለውም ጠቁመዋል።

በታሪኩ ለገሰ