የሀገር ውስጥ ዜና

ለአየር ኃይል ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ ማልበስ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

By Mikias Ayele

February 28, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በያዝነው ዓመት ከፍተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡና በሥራቸው ምሥጉን ለሆኑ 697 የአየር ኃይል አባላት ማዕረግ የማልበስ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ፡፡

ማዕረግ የማልበስ ሥነ-ሥርዓቱን ያከናወኑት የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ናቸው፡፡

በዚሁ መሠረት ለከፍተኛ መኮንኖቹ፤ ከሻምበል ወደ ሻለቃ፣ ከሻለቃ ወደ ሌተናል ኮሎኔል እንዲሁም ከሌተናል ኮሎኔል ወደ ሙሉ ኮሎኔል የማዕረግ ማልበስ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

የማዕረግ ማልበስ ሥነ-ሥርዓቱ የዓድዋ ድልን ምክንያት በማድረግ በአየር ኃይል ግቢ እየተካሄደ ከሚገኘው ስፖርታዊ ውድድር ጎን ለጎን የተከናወነ ነው፡፡

ዋና አዛዡ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዓድዋ ድል ለሠራዊታችን አንድነት፣ አይበገሬነትንና ሀገር ወዳድነትን የሚያስተምር ነው፡፡

አሁን ያለው የመከላከያ ሠራዊትም በነዚህ ሦስት መርሆች ተመስርቶ ድሉን ሊያከበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የማዕረግ ሹመት የተሰጣቸው ከፍተኛ መኮንኖች፤ ሁሉንም መስፈርት ያሟሉና የአመራር ክኅሎት ብቃታቸው ተረጋግጦ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአየር ኃይል ስታፍ አስተባባሪ ብ/ጄኔራል አበበ ተካ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የአየር ኃይል ኹነቶችን በቀጥታ ማስተላለፍ የሚያስችል የሚዲያ ስቱዲዮ ግንባታ፣ ሰው ሠራሽ ኃይቅ፣ የዓሣ ማርቢያ እና መናፈሻ ሥፍራዎች የግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብርም ተከናውኗል፡፡

በዓለምሰገድ አሳዬ