የሀገር ውስጥ ዜና

የዓድዋ ድል ለብሔራዊ ትርክት መሠረት የጣለ የአብሮነት መንፈስ ነው – አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

By Mikias Ayele

March 01, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም የዓድዋ ድል በኅብረብሔራዊ አንድነት የተገኘ ታላቅ ፍሬ፤ በኢትዮጵያዊነት ወኔ የተቀዳጁት ክቡር አክሊልና ለብሔራዊ ትርክት መሠረት የጣለ የአብሮነት መንፈስ ነው ብለዋል፡

የዓድዋ ድል ለአንድ ዓላማ በጽናትና በአብሮነት የመቆም ውጤት ነው ያሉት አፈ ጉባዔው÷ኢትዮጵያዊያን በሀገራዊ አንድነት የማይደራደሩ፣ ላመኑበት ነገር ግንባራቸውን የማያጥፉና ፊታቸውን የማይመልሱ መሆናቸውን በገሃድ ያሳየ የአንድነታችን በዓል ነው ሲሉም ገልፀዋል።

የዓድዋ ድል መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ መደማመጥንና ብሔራዊ ስሜትን የሚያስተምር ታላቅ ተቋም እንደሆነም አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባሕል፣ በቋንቋና በአመለካከት ሊለያዩ ይችላሉ፤ ሆኖም በአንድ እንዲተሙ የሚያደርግ ብሔራዊ የአብሮነት እሴት አላቸው ሲሉ ጠቁመዋል።

ስለሆነም በዘመናት መካከል ፈተናዎችን በድል የተሻገረውንና ለቀሪው ዓለም ትምህርት እየሰጠ የመጣውን መልካም የአብሮነት እሴታችንን ሳናጎድል ከነሁለመናው ልናሻጋግረው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የዓድዋ ድል የጥንት ሥልጣኔና የገናና ስም ባለቤት የነበረችውን ኢትዮጵያ ከዘመናዊ ዓለም ጋር መልሶ ያገናኘ ድልድይ እንደሆነ አመልክተዋል።

ወድቆና ደቆ መቅረት እንጂ ወድቆ መነሳትና ፈርሶ መሠራት መጥፎ ሊባል እንደማይገባ ጠቁመው÷ የጥንቱን ሥልጣኔያችንንና የትናንቱን ዓድዋችንን በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ሕያው ሆነው እንዲቀጥሉ ዛሬያችንን በሁሉም መስክ ማሳመር ይኖርብናል ሲሉ ማስገንዘባቸውን የፌደሬሽን ም/ቤት መረጃ ያመለክታል።