አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ያልተቋጨውን ሕግ የማስከበር ሥራ ለማጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት”ቀበሌዎቻችንን በማጽናት ሁለንተናዊ እምርታ እናስመዘግባለን” በሚል መሪ ሃሳብ ለከተማ እና ገጠር ቀበሌያት አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
በስልጠናው የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት ÷በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ከ4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ስለሆነም የቀበሌ አመራሮች ተማሪዎች ወደ ት/ቤት እንዲመለሱ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
መንግሥት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው÷ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ በድጎማ የተገዙ የግብርና ግብዓቶች ወደ ቀበሌዎች እንዲደርሱ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው ÷ብልጽግና በብዙ መስዋዕትነት የተወለደ ፓርቲ መሆኑን ገልፀው፤ለውጡ በብልሃት እና በቅንጅት በመመራቱ ባለፉት 6 ዓመታት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አሳታፊ እና ኀብረ ብሔራዊ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ በችግር እና ተጽዕኖ ውስጥ ሆኖም የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስኬቶችን አስመዝግቧል ያሉት ሃላፊው÷የልማት ተግዳሮት በሆኑ ሃይሎች ላይ ግን ሕግ የማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለት የተጀመረው የቀበሌ አመራሮች ስልጠና በክልሉ በሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አሥተዳደሮች እና ቀበሌዎች የሚሰጥ ሲሆን÷ስልጠኛው ለ3 ተከታታይ ቀናት ይቆያል መባሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡