የሀገር ውስጥ ዜና

የዓድዋ ድል የውስጡንም፣ የውጩንም የቆረጠ ስለት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Melaku Gedif

March 01, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በዓድዋ ዘመቻ ዋዜማ ኢትዮጵያን ከውጪም ከውስጥም ተቀናጅቶ የማዳከም ዘመቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የውጩ የኢትዮጵያን መኖር የማይፈልግ ጠላት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ የውስጡ ደግሞ ለውጩ ጠላት የሚላላክ ባንዳ ነው፤የውጩ የኢትዮጵያ ስም የሚለወጥበት አጋጣሚ ዕንቅልፍ የሚነሣው ጠላት ነው ብለዋል፡፡

ዓድዋ ባለ ሁለት ስለት ነው፤ የውጩንም የውስጡንም ቆርጧል፤ ኢትዮጵያውያን ሲነሡ የውጭ ባዳ የውስጥ ባንዳ እንደማያግዳቸው አሳይቷል ነው ያሉት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለ129ኛው የዐድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ።

ዐድዋ ውስጡንም ውጩንም የቆረጠ ስለት ነው።

በዐድዋ ዘመቻ ዋዜማ ኢትዮጵያን ከውጭም ከውስጥም ተቀናጅቶ የማዳከም ዘመቻ ነበረ። የውጩ የኢትዮጵያን መኖር የማይፈልግ ጠላት ነው። የውስጡ ደግሞ ለውጩ ጠላት የሚላላክ ባንዳ ነው።የውጩ የኢትዮጵያ ስም የሚለወጥበት አጋጣሚ ዕንቅልፍ የሚነሣው ጠላት ነው።

ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከነጻነት፣ ከአትንኩኝ ባይነት እና ከጥቁር ሕዝብ ክብር ጋር የተሣሠረ ስም ነው። ይሄን ካላጠፋ ዕረፍት የማይገደው፣ ዕንቅልፍ የማይወስደው ጠላት ነው። የውስጡ ሀገር ሲፈርስ ፍርስራሹን በመሸጥ ለመለቃቀም የቋመጠ ተላላኪ ነው።

ዐድዋ ባለ ሁለት ስለት ነው። የውጩንም የውስጡ ቆርጧል። ኢትዮጵያውያን ሲነሡ የውጭ ባዳ የውስጥ ባንዳ እንደማያግዳቸው አሳይቷል።

ኢትዮጵያዊ የተባለው ኅብረ ብሔራዊ ጦር ከትዕግሥት በኋላ ሲነሣ፤ ከፊቱ የሚቆም እንደሌለ አስመስክሯል።

ዐመል በጉያ ተይዞ ይሟገቱበታል እንጂ ሀገር አያፈርሱበትም። ልዩነት ወይ ይከራከሩበታል፣ ወይ ያጌጡበታል እንጂ አይዋጉበትም። ይህ ነው የዐድዋ ዘመቻ ልጆች መርሕ።

ከ100ሺ በላይ ሠራዊት፣ ከመላ ሀገሪቱ ተምሞ፤ ሎጀስቲክሱ በሀገር ዐቅም ተደምሮ፤ በቅሎው ተጭኖ፣ ፈረሱ ተገርቶ፣ ስንቁ ተቋጥሮ፣ ያ ሁሉ ቋንቋ በሀገር ፍቅር ተግባብቶ፣ ተአምር ሠርቷል። ይሄ ነው በሁለት በኩል የሚቆርጠው ሰይፍ።

የዐድዋ ዘመቻ ልጆች ዛሬም አለን። እንታገሣለን። እንለምናለን፤ ንቀን እናልፋለን። በመጨረሻ ግን በሁለት በኩል ለመቁረጥ እንነሣለን።

እንትና ከእንቶኔ ማደማቸው አይገርመንም። እኛ የዐድዋ ዘመቻ ልጆች ነን። የእቴጌ ጣይቱ ቃል ቃላችን ነው።

“እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፡፡ ነገር ግን ሀገሬ እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱ ጨርቅ ያድርግልህ፡፡ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ፣ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ፣ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ፡፡

ሂድ የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሐበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ጊዜ ተመለስ፤ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ጊዜ እናየዋለን፤ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፤›› ነበር ያሉት። ይህ ከብዙ ትዕግሥት በኋላ የመጣ ቁጣ ነው።

ዛሬም ጦርነት አንፈልግም። በቂ የጦርነት ታሪክ አለን። የሚጎድለን የብልጽግና ታሪክ ነው። ስለዚህ ሺ የሰላም መንገዶችን እንሞክራለን። እምቢ ከተባልን ግን፣ ምን እናደርጋለን። እያዘንንም ቢሆን የእቴጌ ጣይቱን መንገድ እንመርጣለን።

በድጋሚ መልካም በዓል ይሁን።