የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የጤና ዘርፍ ሚና የላቀ ነው – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

March 03, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የጤና ዘርፍ ሚና የላቀ ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ ሆሳዕና ከተማ ዓመታዊ የጤና ኤክስቴንሽን ፌስቲቫል ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የዘመኑ ጀግንነት ህዝብን በብቃት ማገልገል እንደሆነ ገልጸዋል።

ለመበልጸግ እና ለማደግ በጤናው መስክ ላይ የሚተገበረው ስራ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው፤ ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ አምራች ኃይል ይሆናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የጤና ዘርፍ ሚና የላቀ ነው በማለት ገልጸው፤ ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ ጤንነቱ የተጠበቀ ትውልድ አስፈላጊ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ እየተተገበረ ያለውን የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ጨምሮ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የጤና ተቋማት ማስፋፋትና የጤና ባለሙያዎችን በጥራትና በብዛት በማሰልጠን የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት ዓመታትም አዲስ የተቀረፀውን የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ-ካርታ ተግባራዊ በማድረግ አገልግሎቱን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።