የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ዮርዳኖስ የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

By Adimasu Aragawu

March 03, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡመር ሁሴን ከዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ አምባሳደር ሞሃመድ አቡ ዊንዲ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት አድርገው መክረዋል፡፡

በዚህም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በፖለቲካዊ ምክክር፣ የጋራ የሚስትሮች ስብሰባ በማካሄድ እና በሀገራቱ መካከል የሥራ ጉብኝት በማድረግ ትብብሩን ማጠናከር እንደሚገባ ተስማምተዋል።

እንዲሁም ሀገራቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተግባብተዋል።

ይህንን ትብብር ለማሳካት ሁለቱ ወገኖች የንግድ ልውውጣቸውን ማሳደግ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፎረም ለማዘጋጀት ተስማምተዋል፡፡

በተጨማሪም ቀጣናዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ በመምከር ገንቢ ሀሳቦችን የተለዋወጡ ሲሆን፤ በውይይት የተግባቡባቸውን ጉዳዮች ወደተግባር ለማስገባት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን አቡ ዳቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡