የሀገር ውስጥ ዜና

ጃይካ በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ድጋፉን እንደሚቀጥል ገለጸ

By Adimasu Aragawu

March 03, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ፕሬዚዳንት ያማጉቺ ሂሮይኪ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በምታደርገው ሂደት ሩዝን በስፋት ማምረት መጀመሯን ገልጸው፤ ኤጀንሲው በሩዝ ልማት ያለውን ልምድ በመጠቀም ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

ጃይካ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሆርቲካልቸርና በሩዝ ልማት፣ በሥርዓተ ምግብና ሌሎች መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑ በወይይቱ ላይ ተነስቷል።

70 በመቶ የሚጠጋው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ የግብርና ምርት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የግብርና ግብይትን ለማጠናከር የኤጀንሲው ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጃይካ ምክትል ፕሬዚዳንት ያማጉቺ ሂሮዩኪ በበኩላቸው÷ ጃይካ ኢትዮሼፕ በተሰኘው ፕሮጀክቱ አማካኝነት በሆርቲካልቸርና በሌሎች ዘርፎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የግብርና ግብይትን ለማጠናከር ድጋፉን እንደሚቀጥል መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡