የሀገር ውስጥ ዜና

ስድስት አትሌቶች ለ2025ቱ ሎረስ ወርልድ ስፖርት አዋርድ በእጩነት ቀረቡ

By Mikias Ayele

March 03, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓሪሱ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የነበሩ ስድስት አትሌቶች ለ2025ቱ ሎረስ ወርልድ ስፖርት አዋርድ በእጩነት መቅረባቸው ተገለፀ፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ እና ለኔዘርላንድስ የምትሮጠው ሲፋን ሀሰን፣ ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕየጎን፣ አሜሪካዊቷ የመሰናከል አትሌት ሲድኒ ማካላፊን ሌቭሮን በምርጥ ሴት አትሌቶች ዘርፍ የቀረቡ እጩዎች ናቸው፡፡

በኦሊምፒኩ ሲፈን ሀሰን በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር ነሀስ በማራቶን ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ፣ ፌዝ ኪፕዮጎን በ1 ሺህ 500 ሜትር ወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር ደግሞ ብር ስታገኝ ሲድኒ ማካላፊን ሌቭሮን በ400 ሜትር መሰናክል የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም የ100 ሜትር ሴቶች አሸናፊዋ ጁሊያን አልፈርድ በ2025ቱ ሎረስ ወርልድ ስፖርት አዋርድ በእጩነት የቀረበች ሌላኛዋ አትሌት ናት፡፡

በኦሊምፒኩ የምርኩዝ ዝላይ ባለ ሪከርዱ ስዊድናዊው ሞንዶ ዱፕላንትስ እና በ200 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን የቻለው ቦትስዋናዊው አትሌት ሌስሊ ቶቦጎ በእጩነት የቀረቡ ወንድ አትሌቶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን በመወከል በፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ክብረ ወሰን በማሻሻል ያሸነፈው ታምራት ቶላ በእጩነት ይቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይካተት ቀርቷል፡፡

የ2025ቱ የሎረስ ምርጥ የዓለም ስፖርት ሽልማት በፈረንጆቹ ሚያዚያ 12 በስፔን ማድሪድ እንደሚካሄድ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመላክታል፡፡