የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመቀነስ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ 

By ዮሐንስ ደርበው

March 04, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማሳደግ የመሠረተ-ልማት መልሶ ግንባታ እና የኃይል ማሻሻል ሥራ እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ለአብነትም ባለፉት ሰባት ወራት 38 ሺህ 855 ኪሎ ሜትር የቅድመ ጥገና ሥራ እና 5 ሺህ 205 ኪሎ ሜትር የመልሶ ግንባታ ሥራ ማከናወኑን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ባለባቸው አካባቢዎች 941 ትራንስፎርመሮች ላይ የኃይል ማሻሻያ ማድረጉን ነው የገለጸው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኃይል አቅርቦቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ 2 ሺህ 1 ትራንስፎርመሮችን ተክያለሁ ብሏል፡፡

የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግም 7 ሺህ 6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዲስትሪቢዩሽን መስመሮች ማስፋፊያ መሥራቱን አንስቷል፡፡

አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖርና የደንበኛ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በትጋት እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው፡፡

በዮሐንስ ደርበው