አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 6 ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ61 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ፥ የኃይል ማመንጨት ሥራ ላይ በትኩረት በመሥራት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
በግማሽ በጀት ዓመትም 11 ሺህ 686 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 13 ሺህ 504 ጊጋ ዋት ማመንጨት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከተመረተው ኃይል ውስጥም ለጅቡቲ 274 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 17 ነጥብ 16 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ለኬንያ 654 ነጥብ 9 ጊጋ ዋት ሰዓት እና ለሱዳን 26 ነጥብ 6 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡
ለሦስቱ ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭም 61 ነጥብ 07 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ