አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲዮ ዞን ዲላ ከተማ ከ348 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ፕሮጀክቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡
ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ፕሮጀክቱ የውሃ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት እያከናወነ ያለውን ስራ ማሳያ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ በ8 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከንፁህ መጠጥ ውሃ ባሻገር ከተሞች ንፅህናና ጥራት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራም በትኩረት እንደሚከናወን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተመረቀው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ዲላ ከተማ የውሃ ተምሳሌት ሆና ሳለ በውሃ የምትቸገር ከተማ የነበረችበትን ሁኔታ የቀየረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ብልጽግና ፓርቲ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል ጉባኤውን ባካሄደ ማግስት መመረቁ ፓርቲው የገባውን ቃል ማሳካት እንደሚችል ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ ወጪ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተሸፈነ ሲሆን ከ192 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
በዓለምሰገድ አሳዬ