አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የቀጣናው ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ሥርዓተ-ምግብ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል ሥርዓተ-ምግብ በመፍጠር ሂደት ያላቸውን ተሞክሮ ለመለዋወጥ እና ትብብራቸውን ለማጠናከር ያለመ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
መርሐ ግብሩን ኢጋድ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የዓለም ባንክና እና የደቡብ አፍሪካ የግብርና ምርምርና ልማት ማስተባበሪያ ማዕከል በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በተወካያቸው የኢጋድ የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ አበባው ቢሆነኝ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት÷ በቀጣናው የሚስተዋለውን በምግብ ራሰን የመቻል ችግር ለመቅረፍ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የጎርፍ አደጋ፣ ድርቅ፣ ግጭቶች እና የግብርና ግብዓት አቅርቦት ችግር በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ኢጋድ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል ሥርዓተ-ምግብ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል፡፡
ሀገራቱ በዘርፉ ያላቸውን ጥሩ ተሞክሮ እንዲለዋወጡና የግብርና ሥርዓታቸውን በማዘመን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ከዓለም ባንክ እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የቀጣናው ሀገራት እርስ በርስ መተባበርና መደጋገፍ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገች መሆኗን ጠቁመው÷ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ውጤት ማስመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡
የቀጣናው ሀገራት የምግብ ሉዓላዊነታቸው ለማረጋገጥ አዳዲስ አሰራሮችን ማበልጸግ፣ በቴክኖሎጂ መታገዝ፣ ጥሩ ተሞክሮዎችን መጋራት እና ተስማሚ ፖሊስዎችን መቅረጽ እንደሚገባቸው በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል ሥርዓተ-ምግብ መፍጠር ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡