አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በአፍሪካ ቀንድ እና በአፍሪካ ስላሉ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደር ቼን ሀይ በበኩላቸው ቻይና ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
በቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም (ፎካክ) ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ተግባር እንዲገቡ ሀገራቸው የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን ተናግረዋል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል በርካታ የከፍተኛ ልዑካን የጉብኝት ልውውጥ መደረጉ በሁሉም ዘርፎች ያለውን ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር እና ውጤታማ እንዲሆን እንዳደረገው ተነስቷል።
እንዲሁም በዓለም አቀፍ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያም የሀሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።