የሀገር ውስጥ ዜና

በኢነርጂ ዘርፍ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸው ተገለጸ

By Hailemaryam Tegegn

March 05, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት በኢነርጂ ዘርፍ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡

ከለውጡ ወዲህ የኃይል ማመንጨት አቅምን በማጠናከርና የጸሐይ ኃይል ማመንጫዎችን በማስፋፋት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ማስፋት ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

በዚህም ከጠቅላላ የህዝብ ብዛት 54 በመቶ የሚሆኑትን የኃይል ተጠቃሚ በማድረግ ከለውጡ ወዲህ ከ6 በመቶ በላይ ዕድገት ተመዝግቧል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ በለውጡ ማግስት ልዩ ክትትል ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች እያደረጉ ያሉትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ የጠቀሱት ሚኒስትሩ÷ በዚህም እንደ ሀገር ኃይል የማመንጨትና የማቅረብ አቅም እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

በኢነርጂው ዘርፍ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ቆጣሪ ያላቸውን ደንበኞች ማፍራት መቻሉንና ባለፉት ስድስት ወራት ከ320 ሺህ በላይ አዳዲስ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በጸሐይ ኃይል ማመንጫ ሶላር አማካኝነት ከዋናው መስመር በራቁ አካባቢዎች ከ10 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡